Amharic Version

ቅልልቦሽ

ታሪካዊ ዳራ

ድቡልቡል የሆኑ ነገሮችን እየወረወሩ መቅለብ ለዘመናት የሰው ልጆችን ሲያዝናና የቆየ ጨዋታ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የዚህ አይነቱ ጨዋታ ቅልልቦሽ ይባላል፡፡ ትውልድ የልጅነት ጊዜ ጨዋታውን እያስታወሰ ከሚደሰትባቸው ትዝታዎች አንዱ ቅልልቦሽ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ቅልልቦሽ አሁንም የቀጣዩ ትውልድ ባህል ሆኖ ቀጥሏል፡፡

አሁን የተዘጋጀው የቅልልቦሽ ጨዋታ ቀደም ካሉት የጨዋታ አይነቶች ይልቅ ፈታኝ ጨዋታ ነው፡፡ የሂሳብ፣አይን እና እጅን ማቀናጀትን እንዲሁም የተጠየቅ(ሎጂክ) ክህሎትንም የሚያዳብር ነው፡፡

መግለጫ

በዚህ ጨዋታ ውስጥ ባለ ብዙ ጎን አምስት ጠጠሮች ይገኛሉ፡፡ ከታች በ(ስእል1) እንደተመለከቱት አራቱ ጠጠሮች ቢጫ ናቸው፤ አንዱ ደግሞ ጥቁር ነው፡፡ አምስት ቁጥር የተጻፈበት ጥቁር ጠጠር አጫዋች ነው፡፡ከ1 እስከ 5 ያሉት ቁጥሮች በጠጠሮቹ ላይ በአረቢክ፣ በግእዝ እንዲሁም በነጠብጣብ መልክ ተጽፈዋል፡፡ በሁሉም ጠጠሮች ላይ ያለው Qb የሁሉም ጠጠሮች የጋራ አርማ ወይም ሎጎ ነው፡፡ በጨዋታው ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ያሉ ሰዎች ተሳታፊ መሆን ይችላሉ፡፡ ይሁንና ቅልልቦሽን ስምንት አመትና ከዚያ በላይ እድሜ ያላቸው ሰዎች ሊጫወቱት ይችላሉ፡፡

(ስእል 1)

የጨዋታው ህግና ደንብ

ስድስት የጨዋታ ተራዎች አሉ፡፡ ሶስቱ ተራዎች በቀኝ እጅ ሶስቱ ደግሞ በግራ እጅ የሚጫወቷቸው ናቸው፡፡

ጨዋታውን ለመጀመር አራቱ ቢጫ ጠጠሮች በእጅ መዳፍ ውስጥ ይያዛሉ፡፡ አንዱ አጫዋች ጠጠር በአውራ ጣት እና በሌባ ጣት ይያዛል፡፡

ሁሉም የጨዋታ ዙሮች ሲጀመሩ አንዱ አጫዋች ጠጠር ወደ ላይ ይወረወርና አራቱ ጠጠሮች መሬት ላይ በጥንቃቄ እንዲበተኑ ይደረጋል፡፡

አጫዋቹን ወደ ላይ የምንወረውርበት ርቀት መሬት ላይ የበተንናቸውን ጠጠሮች ለቅመን ወደላይ የወረወርነውን ጠጠር መልሰን ለመቅለብ የሚያስችለንን ጊዜ ተምነን ሊሆን ይገባል፡፡ በመሆኑም አጫዋቹን ከፍ አድርገን በወረወርን ቁጥር መሬጽ የጣልናቸውን ጠጠሮች ለቅመን አጫዋቹ መሬት ሳይወድቅ መልሰን ለመቅለብ ሰፊ ጊዜ ማግኘት እንደምንችል ማሰብ ይገባናል፡፡

የመጀመሪያ ዙር( በአንድ ጊዜ አንድ ጠጠር መልቀም)፡- አጫዋቹን ወደላይ እየወረወርን መሬት ላይ ከተበተኑትን አራት ጠጠሮች መካከል አንድ አንዱን መልቀም ነው፡፡ ይህን ጨዋታ አራቱም ጠጠሮች እስኪያልቁ ድረስ እንደግመዋለን፡፡ የሚለቀሙት ጠጠሮች በአንድ መዳፍ ውስጥ መቆየት አለባቸው፡፡ በጨዋታ ሂደት ውስጥ አጫዋቹ ጠጠር ከእጅ አምልጦ መሬት ከነካ ጨዋታው እንደከሸፈ፤ ተጫዋቹም እድሉን እንዳበላሸ ይቆጠራል፡፡

ውጤት አመዘጋገብ፡

ጨዋታው ሳይከሽፍ የለቀምናቸው ቢጫ ጠጠሮች ላይ ያሉ ቁጥሮች ይደመሩና በአንድ ይባዛሉ፡፡

ለምሳሌ፡ 10X1 = 10

ሁለተኛ ዙር፡ (በአንድ ጊዜ ሁለት ጠጠር መልቀም) በጨዋታው የተለቀሙ ቢጫ ጠጠሮች ላይ ያሉ ቁጥሮች በመጀመሪያው ዙር ከተገኘ ነጥብ ጋር ይደመራል፡፡ በዚህ ጨዋታ ሙሉ ሙሉ ቁጥሮች ወይም ጎዶሎ ጎዶሎ ቁጥሮች ያሉባቸውን ሁለት ጠጠሮች በአንድ ላይ የለቀመ የጉርሻ (የቦነስ) ነጥብ ያገኛል፡፡

የውጤት አመዘጋገብ፡ የተለቀሙት ቢጫ ጠጠሮች ላይ ያሉ ቁጥሮች ይደመሩና በሁለት ይባዛሉ፡፡

ለምሳሌ፡ 10X2 = 20

ስለዚህ 20(የሁለተኛ ዙር) + 10(ጉርሻ)= 30 ነጥብ

ሶስተኛ ዙር፡ (በአንድ ጊዜ አራት ጠጠር መልቀም)፤ በዚህ ዙር አራቱንም ጠጠር መልቀም ካልተቻለ ምንም ነጥብ አይሰጥም፡፡

የውጤት አመዘጋገብ፡

በዚህ ዙር አራቱም ጠጠሮች በአንድ ጊዜ ከተለቀሙ ቢጫዎቹ ጠጠሮች ላይ ያሉ ቁጥሮች ተደምረው በሶስት ይባዛሉ፡፡ በመሆኑም አጠቃላይ ውጤቱ እንደሚከተለው ይሰላል፡፡

3X10 = 30 (የሶስተኛ ዙር ውጤት)

30 + 10 (የመጀመሪያ ዙር) + 20 (የሁለተኛ ዙር) = 60 ነጥብ (ይህ ውጤት ጉርሻ ካልተገኘ የሚመጣ ውጤት ነው)

የመጨረሻ ዙር፡

አጫዋቹን ጠጠር ጨምሮ አምስት ጠጠሮች በአንድነት ይያዛሉ፡፡ አምስቱንም ጠጠሮች በጥንቃቄ በአንድ ላይ ወርውረን በመዳፋችን ጀርባ ላይ እንዲያርፉ እናደርጋለን፡፤ እንደገና ጠጠሮቹን መልስን በእጃችን መዳፍ እንቀልባቸዋለን፡፡

የውጤት አመዘጋገብ፡

አጫዋቹን ጨምር የእጃችን መዳፍ ጀርባ ላይ አሳርፈን መልሰን የቀለብናቸው ጠጠሮች ላይ ያሉ ቁጥሮች ይደመሩና በአራት ይባዛሉ፡፡

ለምሳሌ ሁሉንም ጠጠሮች ከቀለብን ውጤቱ 4X15 = 60

የአራቱም ዙር አጠቃላይ ድምር እንደሚከተለው ይሆናል፤

10 (መጀመሪያው ዙር) + 20 (የሁለተኛው ዙር) + 30 (የሶስተኛው ዙር) + 60 (የመጨረሻ ዙር) = 110 ነጥብ

አንድ የጨዋታ ተራ ሲያልቅ ሌላኛው ተጫዋች ይተካል፡፡ ተጫዋቾች ተራ ሲደርሳቸው እጃቸውን እያለዋወጡ በመጀመሪያው ተራ በቀኝ እጅ በሁለኛው ተራ በግራ እጅ እያለዋወጡ ይጫወታሉ፡፡

በየትኛውም ዙር የተበተኑንት ጠጠሮች ለመልቀም ሙከራ በሚደረግበት ጊዜ ወደላይ የወረወርነው አጫዋች ጠጠር ከእጃችን አምልጦ መሬት ከነካ ጨዋታውን እንደፎረሽን ይቆጠራል፡፡

ትልቁ ጉርሻ ፤

በዚህ ጨዋታ ትልቁ ጉርሻ ወይም ቦነስ የሚሰጠው ለመልቀም መሬት ላይ የበተንናቸው ሁሉም ጠጠሮች ላይ የጨዋታው አርማ ወይም ሎጎ የሆነው Qb በተመሳሳይ ጊዜ የሚታይ ከሆነ ትልቁን ጉርሻ (120) ነጥብ ተጫዋቹ ያገኛል፡፡

አንድ ሙሉ የጨዋታ ተራ የመጀመሪያ ዘር ጉርሻን ጨምሮ ምንም ሳይፎረሽ መጫወት ከተቻለ የሚገኘው ነጥብ 120 ይሆናል፡፡